ጸሎተ ፍትሐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናን፤
ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት መፍታት ወይም መፈታት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው ጸሎት ጸሎተ ፍትሐት ይባላል።
የሙታን ነፍሳት ከሥጋ እንደተለዩ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ በማረፊያ ቦታ ይቆያሉ እንጂ በቀጥታ ወደ መንግስተ ሰማይ ወይም ወደ ገሃነመ እሳት እንደማይላኩ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውና የምታስተምረው ትምህርት ነው፤ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚቆዩበትም ቦታ ለጻድቃን ገነት ሲሆን ለኃጢአተኞች ደግሞ ሲኦል ነው። የጻድቃን ማረፊያ ቦታቸው ገነት መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በነበረ ጊዜ ንስሐ ለገባው ወንበዴ፡ “በእውነት እልሃለው ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። ሉቃስ ፳፫፡ ፵፫። የኃጢአተኞች መቆያ ደግሞ ሲኦል መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሀብታሙ ሰውና በድኻው አልዓዛር ምሳሌ ትምህርቱ ሀብታሙ ሰው በሲኦል ውስጥ እንደነበረ ገልጿል። ሉቃስ ፲፮፡ ፳፫፡፡
በሙታን ትንሣኤ ጊዜ የምንነሳው በውርደት ወይም ክብር በሌለው ሁናቴ በመሬት ውስጥ እንደተቀበርነው ሳይሆን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በክብር፣ በኃይልና በመንፈሳዊነት ነው። ፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፡ ፵፪-፵፬። ከዚያም በኋላ ወደ ክርስቶስ የፍርድ ፊት እንቀርባለን። ፪ኛ ቆሮንቶስ ፭፡ ፲፤ ራዕይ ፮፡ ፱-፲፩፡፡
ይቅርታ በዚሁ ዓለምና በሚመጣውም ዓለም መኖሩን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል። ማቴዎስ ፲፪፡ ፴፪፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ለነበረው ለኦኔሲፎር “በመጨረሻው ቀን ምሕረትን ይስጠው” ብሎ ጸልዮለታል። ፪ኛ ጢሞቴዎስ ፩፡ ፲፰። ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ጸሎት ለሞቱ ሁሉ ትጸልያለች።
ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ደግሞ በጥንት በዘመነ ብሉይም ነበረ። ጀግናው ይሁዳ መቃብዮስ በጦርነት ለሞቱ ወታደሮቹ የኃጢአት መሥዋዕት ይደረግላቸው ዘንድ ሁለት ሺህ የብር ድራህም አሰባስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ልኳል። ፪ኛ መቃብያን ፲፪፡ ፵፫፤ ዕዝራ ሱቱኤል ፮: ፴፭። አይሁድ ለሙታን ሲጸልዩ ዳዊት ይደግማሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በተላከው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ ባደረገው ስብከቱ እንዲህ ብሏል “አንድ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ቢሞት የምንችለውን ያኽል ልንረዳው ይገባል። የምንረዳውም በለቅሶና በሐዘን ሳይሆን በጸሎት፣ በምጽዋትና በቁርባን ነው። የዓለምን ኃጢአት ወደ ተሸከመው የእግዚአብሔር በግ ስለ ሙታን የምንጸልየው እነርሱ መጽናናትንና እረፍትን እንዲያገኙ ብለን ነው እንጂ በከንቱ አይደለም። ጻድቁ ኢዮብ ስለልጆቹ ያቀርብ የነበረው ቁርባን ጠቀሜታ ከነበረው ስለ ሙታን የምናቀርበው ቁርባን ምንኛ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረው?
እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይቀበልልን!
ሚያዝያ 2020