የጥምቀት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናን፤
ጥምቀት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል። ጥምቀት አንድ ምዕመን እንደገና ከመንፈስ ቅዱስ ልደት የሚያገኝበትና የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆንበት የመጀመሪያው መግቢያ በር ነው። ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፣ ፭ ላይ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ” በማለት የአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ልብ ላለው ጥምቀት በጌታችን ትምህርት መመሥረቷን ይስረዳል።
በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥምቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገም ገልጦ ተናግሯል (ኤፌ.፬፣ ፭)። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፥ በቁስጥንጥንያ በ ፫፻፹፩ ዓ.ም. የተሰበሰቡ ፩፻፶ የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት፣ ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኃጢአትን በደልን የምታርቅ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፤ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል።
ጥምቀት አንድ ምዕመን እንደገና ከመንፈስ ቅዱስ ልደት የሚያገኝበትና የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆንበት የመጀመሪያው መግቢያ በር ነው። ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፣ ፭ ላይ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ” በማለት የአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ልብ ላለው ጥምቀት በጌታችን ትምህርት መመሥረቷን ይስረዳል።
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ወንድ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴት በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የጥምቀት ሥርዓት ይፈጸምላቸዋል። የህጻኑ ጤንነት የሚያሰጋ ከሆነ ከዚህ ቀን በፊትም ሊፈጸም ይችላል። በችግርና በሌላ ምክንያት ከተጠቀሰው ቀን ቢዘገይ ቤ/ክ የመጡትን ወደኋላ አትመልስም ታጠምቃለች። በ ፵ እና በ ፹ ቀን የሆነበት የመጀመሪያው ምክንያት አዳም በተፈጠረ በ ፵ ቀን ሔዋን በተፈጠረች በ ፹ ቀን ገነት እንዲገቡ ስለተፈቀደላቸው ነው (ኩፋ ፬፣ ፱)። ሌላው ደግሞ በኦሪት ሕግ ወንድ በተወለደ በ ፵ ቀን ሴት በ ፹ ቀን ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው ቡራኬ ተቀብለው በርግብና በዋኖስ ደም ተረጭተው ከዕብራውያን መዝገብ ገብተው ይመለሱ ነበር። በኦሪት ይደረግ የነበረው ሥርዓት ለሐዲስ ምሳሌ በመሆኑ በዚሁ በኦሪት ልማድ መሰረት ልጆችም እንደየጾታቸው በ ፵ እና በ ፹ ቀን በመጠመቅ የጸጋ ልጅነት ያገኛሉና ነው (ዘሌ ፲፪፣ ፩=፰፤ ሉቃ ፪፣ ፳፪)። ሐዋርያትም በአገልግሎት ዘመናቸው የክርስቶስን ትምህርት በመከተል የእድሜ ልዩነት ሳያደርጉ ሕዝብን ሁሉና በአንድ ቤት የሚገኙ የቤተሰብ አባላትን በሙሉ ያጠምቁ ነበር (የሐዋ ፲፣፴፫ ፤ ፩ቆሮ ፩፣፲፮)
የሥርዓተ ጥምቀትን ትርጉምና የመሠረተው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆኑ በአጭሩ ከገለጽን፤ ጌታችን የተጠመቀው ለምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሣ ጌታችን እርሱ ባወቀ ጥምቀትን የፈጸመበት ዋነኛ ምክንያቶች እንደ ሊቃውንት አባቶቻችን አስተምህሮ በሦስት መንገዶች ይታያል። እነዚህም፦
፩ኛ) ምሥጢረ ሥላሴን/ሦስትነቱን ያስረዳን ዘንድ (ማቴ. ፫፣ ፲፫-፲፯)
፪ኛ) ለትምህርት፡ ለትህትናና ለአርዓያነት (ዮሐ. ፲፫፣ ፩-፲፯ እና ፩ኛ ጴጥ. ፪፣ ፳፮)
፫ኛ) ጥምቀታችንን ይባርክልን ዘንድ (ማቴ. ፬፣ ፩-፲) ናቸው።
የልጅነት ጸጋን እናገኝ ዘንድ፡ ዮሐ. ፩፣ ፭
አስቀድመን በሥጋ ከእናትና አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በጥምቀት (በማየ ገቦ ስንጠመቅ) ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን። ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፣ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ያለው (ዮሐ. ፫፣ ፫ እና ፮)። በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል። ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን ወይም የምንጣራበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል” ብሏል (ሮሜ.፰፣ ፲፭-፲፮)። ጌታችንንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል (ዮሐ.፩፣ ፩-፲፫)።
ሥርየተ ኃጢያትን ለማግኘት፡ ሐዋ. ፪፡ ፴፯-፴፰
ከላይ እነደተገለጠው በጌታችን ትምህርት መሰረት (ዮሐ. ፫፣ ፭) ሰዎች ከነበረባቸው ኃጢአት ይነፁ ዘንድ እና ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይገቡ ዘንድ ሥርዓተ ጥምቀት ተሠርታለች። ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በ፶ኛው ቀን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብቱ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ማደሩን የሰሙ አይሁድ ከቅዱሳን ሐዋርየት ዘንድ ቀርበው የሚናገሩትን ቃለ እግዚአብሔር መስማት ጀመሩ። ቅዱሳን ሐዋርያትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነቱን በኃይለ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ወደ ሰማይ ማረጉን ነገሯቸው።አይሁድም ይህንን በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” አላቸው። ይህ የሐዋርያው ቃል የሚያስረዳን የጥምቀትን መድኀኒትነት ነው። አስቀድመን እንደገለጥነው አባቶቻችን በሃይማኖት መግለጫቸው “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፥ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ማለታቸው ጥምቀት ከደዌ ነፍስ የምታድን መሆኗን መመስከራቸው ነው።
ዘላለማዊ ድህነትን እናገኝ ዘንድ ነው፡ ማር. ፲፮፣ ፲፭-፲፮
የሰው ልጅ ድኅነት ቅጽበታዊ አለመሆኑ የታወቀ ነው። ይሁንና የድኅነት በር ከፋችና ሌሎችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለመፈጸም የሚያበቃን ሚስጢር ጥምቀት ነው። ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ መመሪያ ውስጥ በግልጥ ተቀምጧል። “ሑሩ ውስተ ኲሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት። ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ይደየን። ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል” (ማር. ፲፮፣ ፲፭-፲፮)።
ስለዚህ ጌታችን ባስተማረው መሰረት ማንኛውም ሰው ወደመንግስተ ሰማያት መግባት ይችል ዘንድ በሥርዓተ ጥምቀት ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድና የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ይገባዋል። እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ። ይኸውም የመጀመሪያው በሥጋ ከእናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን መሆን ያስፈልገዋል። ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና። እንግዲህ በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋና ክብር ሁላችን ልናስብ ያስፈልገናል። ይህንንም ክብራችንን መጠበቅ ያሻናል።
በኦታዋና ጋቲኖ አካባቢ የምትኖሩና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተካታዮች የሆናችሁ ምዕመናን ከላይ በተገለጸው እምነትና ስርዓት መሰረት ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር በመገናኘት በነጻ የሥርዓተ ጥምቀት አገልግሎት ለማግኘት የምትችሉ መሆኑን እየገለጽን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የሚመጡትን ሁሉ ለመቀበል የፍቅር እጆቿን ዘወትር ዘርግታ ትጠብቃለች።
ይህን ቅጽ ሞልተው ለሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ከ 1 ሳምንት በፊት ያስረክቡ