Establishment

የደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አመሰራረት ፡ጉዞ እና አደረጃጀት በአጭሩ፦

በስመ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አሜን!

አመሰራረት እና ጉዞ

ቤተክርስቲያናችን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም በፈቃደ እግዚአብሄር በካናዳ ሃገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ በብጹዕ አባታችን አቡነ ማትያስ መልካም ፈቃድና በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ መከፋፈልና ውግዘት ምክንያት በቤቱ ተወስኖ የነበረው ህዝበ ክርስቲያን ይገለገልበት ዘንድ የካቲት 2007 ዓ.ም.  አድራሻው (15 Lebreton St. North, Ottawa, ON) በሚገኘው ‘Annunciation Orthodox Cathedral’ ቤተክርስቲያን ተመሰረተች፡፡ 

ኋላም ለአንድ ዓመት ከአራት ወር አካባቢ በ (397 Kent St. Ottawa, ON) ላይ በሚገኘው የቻይና ኮሚኒቲ ህንጻ ላይ እስከ ሰኔ 7/2009 ዓ.ም. ስንገለገል ቆይተን ቦታው ለአገልግሎት አስቸጋሪ በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ ወደ ተመሰረተችበት ወደቀድሞ ቦታ በመመለስ ከሰኔ 2009 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም.  በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተወስነን ለ (8) ዓመታት ያክል ከተገለገልን በኋላ ቤተክርስቲያኗ አሁን ያለችበትን በ (144 Rue Jean Rene Monette, Gatineau, QC) የሚገኘውን ህንጻ በሐምሌ 2018 ዓ.ም. በእግዚአብሄር ቸርነት፤ በምእመናን ልፋትና እንዲሁም ጥረት ገዝተን ለመግባት ችለናል፡፡ 

በዚህ ጉዞ ውስጥ ቤተክርስቲያናችን ተዘርዝሮ የማያልቅ አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በሰኔ 2008 ዓ.ም.  ቤተክርስቲያናችንን የገጠማት ችግር ግን ቀላል የማይባል፤ ህዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነና ያስለቀሰ እኩይ ተግባር ነበር፡፡ በድፍረት፤ የተሰጣቸውን የእረኝነት ኃላፊነት ወደጎን በመተው፡ የራሳቸውን ጥቅም በሚያስቀድሙ፤ ለመንጋው በማይራሩ እረኞች መሳይ፤ ነውራቸው ክብራቸው፤ ሆዳቸው ደግሞ አምላካቸው በሆነባቸው፡ የቤተክርስቲያኗ ኪዳን ጽላት፤ ታቦተ ህጓን እና ነዋይ ቅድሳቷ በድፍረት ተዘርፎ የነበረበት አሳዛኝ የሆነ ወቅት ነበር፡፡ ይሁንና በእግዚአብሄር አጋዥነት፡ በአባቶች ጸሎትና ብርታት እንዲሁም በቁጥር አነስትኛ በሆነ ነገር ግን ጠንካራ፡ ለፈተና በማይበገር ምእመናንን እንዲሁም  በእግዚአብሄር በጎ ፈቃድ የተዘረፈባት የኪዳን ጽላትም ሆነ ታቦተ ህጓ ሊመለስ ችሏል፡፡

ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ያገለገሉንን ሁሉ መዘርዘር ባንችልም ለረጂም ጊዜ በትጋት ላገለገሉን መላከህይወት ሃረገዎይን ከቶሮንቶ ፤ መላከ መዊ አባ ገብረክርስቶስ ከለንደን ኦንታሪዮ ፤ እና ቀሲስ አላዛር ተሰማ ከኪችነር ርቀትና የአየር ጠባይ ሳይበግራቸው፤ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየተመላለሱ በማገልገል እስከሁን ላደረጉልን እውነተኛ አባታዊ ቡራኬ እግዚአብሄር ረጅም እድሜና እንዲሁም ጤና ይስጥልን፤አገልግሎታቸውንም ይባርክልን፡፡

የዛሬው መላከጺዮን ቀሲስ ጌቱ ረጋሳ በድቁና ማዕረግ ከመጀመሪያው ጀምሮ ምእመኑ እንዳይበተን በማስተማር፤ በመምከር እንዲሁም መዘምራንን በማጠናከር እስካሁን ድረስ ያለ ምንም ምድራዊ ዋጋ ለሰማያዊ በረከት ብቻ በማገልገል ላይ የሚገኙ መልካም አባትና ወንድም ሲሆኑ እሳቸውም ለዚች ቤተክርስቲያን እዚህ መድረስ ዋነኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ስለሆነ እግዚአብሄር ረጂም እድሜና ጤና ይስጥልን፤ አገልግሎታቸውንም ይባርክልን፡፡

በአባታችን መላከ ምህረት ሃይለገብረኤል ኪዳኔ የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪ ሆነው ከተሾሙበት ከሰኔ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ቁጠራቸው አነሰ ፤ ቦታው አይመችም ሳይሉ ከምእመኑ ጋር ችግሩንና መከራውን አልፈነው ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት ዋነኛ አስተዋጽኦ ስላደረጉ እግዚአብሄር ረጂም እድሜና ጤና ይስጥልን እንላለን፤ አገልግሎትዎንም ይባርክልን፡፡

ዛሬ ለእግዚአብሄር ክብር ምስጋና ይግባውና ቤተክርስቲያናችን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም በአንድ ካህንና በሰባት ዲያቆናት ሙሉ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስለምትገኝ ለዚህ ፍሬ ላበቁን ከላይ ለተጠቀሱትና  ላልተጠቀሱትም ጭምር ታላቅ ምስጋናን በእግዚያብሄር ስም እናቀርባለን፡፡  

ዛሬ ሳንሳቀቅ የምንገለገልበትን የራሳችን ህንጻ ቤተክርስቲያን እግዚአብሄር ስለሰጠን ለእርሱ ክብርና ምስጋና ይሁን እያልን ለዚህ ደሞ ላበቁን ጠንካራ ምእመናንና ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ላገለገሉ ሁሉ ድካማቸውን እግዚያብሄር ይክፈልልን እንላለን።

አደረጃጀት

የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከተመሰረተች በሁዋላ

  • ከሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በ Ministry of Government Service Ontario በኦንታሪዮ ግዛት Incorporated በመሆን ተመዝግባለች፡፡
  • ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በበጎ አድራጎት የ (Charity Organization) መስፈርቶችን አሟልታ በ Non-Profit-Charity Organization ዘርፍ ተመዝግባለች፡፡ 
  • ከነሃሴ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ከኦንታሪዮ አልፋ በመላው ካናዳ ትስፋፋ ዘንድ በፌደራል ደረጃ ከፍ ብላ ተመዝግባለች፡፡

ቤተክርስቲያናችን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም የካናዳ ግዛት ውስጥ ቅርንጫፍ መክፈት፤ ወይም አገልግሎቷን ማስፋፋት እንድትችል ሙሉ ፈቃድ ያላት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኩቤክ ግዛት በሚገኘው በጋቲኖ ከተማ ውስጥ የመገልገያ ህንጻ ገዝታ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስትገኝ ፡ በኩቤክ ህግ መሰረት የኢንተርፕራይዝነት ፈቃድ ተሰጥቷት በጋቲኖ፤ኤልመርና ኦታዋ አካባቢ ለሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ግልጋሎትን እየሰጠች ትገኛለች፡፡

ሁሉም ጊዜያት እ/አ/አ ናችው

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!!


ሚያዝያ 2020