የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ
በስመ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አሜን!
እግዚአብሄር ፍጥረታትን በሚፈጥርበት ጊዜ ከፈጠራቸው ፍጥረታት በይበልጥ የሰውን ልጅ ወይም አዳምን ከሁሉም የላቀ አድርጎ እንደፈጠረው ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ። ከዚያም በላይ አዳም በኃጥያት ወድቆ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ምን ያህል እንደወደደውና እንዳከበረው ለሁለተኛ ጊዜ በልደቱና በሞቱ እንዲሁም በትንሳዔው አረጋግጧል።
ቤተ ክርስቲያንን ክርስቶስ በደሙ ሲመሰርታት ሰዎች በክርስቶስ አምነው ከስላሴ ልጅነትን አግኝተው ሰማያዊት እየሩሳሌምን እንዲወርሱ ነው። ስለዚህ ምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያን የሰማያዊቷ እየሩሳሌም ምሳሌ ናት። ሰዎች በሰማያዊት ኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኑሮ በዚህ ምድር እያሉ የቅድስና እና የንጽህናን ህይወት የሚለማመዱባት ቦታ ናት።
ቤተ ክርስቲያን በመድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በክርስትና ህይወት መቆየታቸውና እና ክርስትናን ሲያስፋፉ መኖራችውን ታሪክ ይመሰክራል። አሁን በዘመናችን የምናየው ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ትውፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን ጥንታዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ለሁለት ሺህ ዘመናት ያህል የኢትዮጵያን ማህበረሰብ በኃይማኖት አንጻ፣ በምግባር አሳድጋ በህዝቦቿ መካከል ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን አስፍና ክርስትያኖች ያለምንም የዘር እና የኃይማኖት አድሎ ከማንኛውም የአዳም ልጆች ጋር መኖር እንዲችሉ አድርጋለች።
ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ አስርተ አመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ምክንያት ወደተለያዩ የአለም ክፍሎች መሄድ ሲጀምሩ አጽናኝ እና ሰላም ሰጪ ሆና የተገኘች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ነች። ወደ ውጭው አለም ካህናትን እና አገልጋዮችን በመላክ ምዕመናንን ስታስተምር፣ ስታጽናና እና ስታሰባስብ ቆይታለች። በተለይም ደግሞ በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋና ጋቲኖ አካባቢ ከ2007ዓም ጀምሮ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ለልጆቻቸው ታላቅ ኃይማኖታዊ እና ማህበራዊ አገልግሎትን ስትሰጥ ቆይታለች።
በኦታዋ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከምትሰጣቸው መንፈሳዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች መካከል ምዕመናንን በሃይማኖት በማነጽ ታላቅ መንፈሳዊ ተስፋ እንዲሰንቁ በማድረግ በስራ በርትተው ጤናማ እና ብቁ ታታሪ ሰራተኞች እንዲሆኑ ስታበረታታ ቆይታለች። በተጨማሪም ከትውልደ ኢትዮጵያውያን የተወለዱ ህጻናትን በኃይማኖት በማሳደግ የቤተ ክርስትያናቸውን ትውፊት እና እምነት እንዲይዙ እና በሃይማኖት እና በምግባር እንዲታነጹ በማድረግ ላይ ናት። ቤተክርስትያናችን ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ መጠን፤ የራስዋ ቋንቋ እና ፊደል ያላት በመሆኗ ህጻናቱ ባህላቸውን እና ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ታላቅ አስተውጽኦ እያበረከተች ትገኛለች። በአጠቃላይ በኦታዋና ጋቲኖ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስትያን ትልቁ አላማዋ ምዕመናን በሀይማኖት ጸንተው የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርሱ ማዘጋጀት ሲሆን አብይ ተልዕኮዋም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን እምነት፣ ሥርዓትና ታሪክ በማስተማርና ሚስጢራተ ቤተ ክርስትያንን በመፈጸም ምዕመናን ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር በመተባበር ለኦታዋና እና ለአካባቢው እንዲሁም ለትውልድ ሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
አሜን!
ሚያዝያ 2020