ቅዱሳት መጻሕፍት
በስመ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አሜን!
‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮)
ምንባባት, ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን, ስብከት, ቅዱሳት መጻሕፍት, ትምህርተ ሃይማኖት, አጽዋማት, ክርስቲያናዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር, ወቅታዊ ትምህርት
በዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት በእለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ ይህን ባለመውደዱም የገመድ ጅራፍ ካበጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮) ከዚህ በኋላ ጌታችን በአይሁድ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም የተሰበሰቡትንም ዝም ይሉ ዘንድ ከገሠፃቸው በኋላ አስተማራቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ‹‹ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡›› እነርሱም ወደ ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ። በዚህ ወቅት ጌታችን ወንጌልን ባስተማረው መሠረት እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተመዘገበውም እንዲህ ይነበባል፡፡ እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡ (ቆላ. ፪÷፲፮) ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡ (ያዕ. ፪፥፲፬) ነገር ግን አንድ ሰው÷ “አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን? “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጒበኞችን ተቀብላ÷ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ÷ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡ በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ “ቆርኔሌዎስ ሆይ÷” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ “አቤቱ÷ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” (የሐዋ.፲፥፩-፰)ምንባባት
ግብረ ሐዋርያት
እግዚአብሔር አምላክ ምሕረት ይሰጠን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፤
አዋልድ መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያላቸው ተዛምዶ፡–
ቀደም ተብሎ እንደተለጠው አዋልድ መጻሕፍት ልጅነታቸው ለአሥራው መጻሕፍት (ለመጻሕፍት አምላካውያት) ነው፡፡ ልጅ ከአባቱ አብራክ፣ ከእናቱ ማኅጸን ተከፍሎ ወላጆቹንመስሎ እንዲወጣ እነዚህም በምሥጢርም በእምነትም በሥርአትም የአሥራውን መጻሕፍት ሥርና መሠረት ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በምሥጢርም ኾነ በሥርዓት ከአሥራው መጻሕፍት ጋር የሚቃረኑት መጻሕፍት ከአዋልድ አይቆጠሩም፡፡ ምክንያቱም በሐዋርያው ቃል “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን” ተብሏልና (ገላ.፩፥፰)፡፡
አዋልድ መጻሕፍት ከአሥራው መጻሕፍት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሚከተሉት ነጥቦች መረዳት ይቻላል፡፡
ሀ. በዓይነታቸው፡- አሥራው መጻሕፍት ተብለው የሚታወቁት ሰማንያ አንዱ መጻሕፍት የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብ፣ የትንቢት ተብለው ይመደባሉ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ አዋልድ መጻሕፍት በዚሁ አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህንን የማሳያ ሰንጠረዥ እንመልከት፡-
የመጻሕፍቱ ዓይነት |
የመጻሕፍቱ ይዘት |
|||
የሕግ | የታሪክ | የጥበብ | የትንቢት | |
አሥራው | ብሔረ ኦሪት | መጽሐፈ ሳሙኤል | መዝሙረ ዳዊት | ትንቢተ ኢሳይያስ |
አዋልድ | ፍትሐ ነገሥት | ተአምረ ማርያም | ውዳሴ ማርያም | ፍካሬ ኢየሱስ |
ለ. በባለቤታቸው፡-የቅዱሳት መጻሕፍት ባለቤታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ገንዘቦች፣ በእርሱም ፈቃድና ምሪት የተፃፉ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት በምድር የእግዚአብሔር እንደራሴ የሆነች፣ የጸጋው ግምጅ ቤት ናት (የሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ስለሆነም ከእግዚአብሔር የተላኩ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ወንጌልንና መልእክታትን የጻፉት ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
የአዋልድ መጻሕፍት ጸሐፊዎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሲሆኑ እነርሱም መንፈሰ እግዚአብሔር እንደገለጠላቸው መጠን መጻፍቱን የጻፉት ለቤተክርስቲያን ልጆች ለምእመናን ነው፡፡ በመሆኑም ባለቤታቸው ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ለትርጉማቸው፣ ለታሪካቸውና ለምሥጢራቸው መጠየቅ ያለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ሐ. በቅድስናቸው፡- አሥራው መጻሕፍትንም ሆነ አዋልድ መጻሕፍትን ያጻፈው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የአሥራው መጻሕፍትን ጸሐፍት እንደመረጠ እንዳተጋ ምሥጢር እንደገለጠላቸው፣ የአዋልድ መጻሕፍትን ጸሐፍት የመረጠ፣ ያተጋ፤ ምሥጢር የገለጠላቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ከአንዱ ምንጭ ከመንፈስ ቅዱስ በመገኘታቸውም የአሥራውም ሆኑ የአዋልድ መጻሕፍት ዓላማቸው ነገረ ሃይማኖትን ማስረዳት ደግሞም ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር መጥቀም ነው፡፡(፪ኛ.ጢሞ.፫፥፲፮)
በልዩ ልዩ ዘመናትና ሰዎች በተራራቀ ሀገር ተጽፈው ለየብቻቸው የነበሩትን አሥራው መጻሕፍት ከመሠረተ ሃይማኖት አንጻር መርምራ አረጋግጣ በአሥራው መጻሕፍትነት የተቀበለችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አዋልድ መጻሕፍትንም የምትቀበለው በተመሳሳይ መልኩ ከትምህርቷ አንፃር መርምራ አረጋግጣ ነው፡፡
መ. የእግዚአብሔርን ሥራ በመግለጥ፡- የቅዱሳት መጻሕፍት ተቀዳሚ ዓላማ የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀጥታ ራሱ ወይም በወዳጆቹ አድሮ ለሕዝቡ ያደረገውን ተአምር፣ መግቦት፣ ቸርነት ያብራራሉ፡፡ይህ እውነታ በአሥራው መጻሕፍት በስፋትና በይፋ የተገለጠ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ከመሆኑ የተነሣ የእግዚአብሔር ሥራ ተአምር የተፈጸመላቸውንና የተፈጸመባቸውን ሰዎች፣ ቦታዎች እምብዛም ትኩረት አይሰጧቸውም፡፡ ተአምሩን ብቻ ገልጠው የሰዎችንና የቦታዎችንስምእገሌ፣አንድሰው ብለው ያልፋሉ፡፡ (ማቴ.፳፮፥፲፰፣፩ኛ. ነገ፲፫፥፩፣ ማቴ.፰፥፪፣ ሉቃ.፲፩፥፲፭) ይህ በአሥራው መጻሕፍት ብቻ የሚንጸባረቅ ሳይሆን የአዋልድ መጻሕፍትም ዓላማ ነው፡፡ በገድለ ተክለሃይማኖት፣ በገድለ ጊዮርጊስ፣ በተአምረ ማርያም ውስጥ በቅዱሳን አማላጅነት የእግዚአብሔር ሥራ (ተአምር) የተፈጸመላቸው ወይም የተፈጸመባቸው ሰዎችን ስም፣ ቦታ ሳያነሡ እገሌ፤ እገሊት አንድ ሰው ብለው የሚጠሩት ሰዎቹና ቦታዎቹ መጠሪያ ስለሌላቸው ሳይሆን ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ስለሆነ ነው፡፡
ሠ. የሃይማኖትን ታላቅነት በመግለጥ፡- ቅዱሳት መጻሕፍት በሃይማኖት፣ ለሃይማኖት፣ ስለሃይማኖት የተጻፉ ናቸው፡፡ ከጥርጥር፣ ከአጉል አሳብ ተጠብቆ በመጻሕፍቱ የተገለጠውን፣ የታዘዘውን ለጠበቀ የተባለው ይፈጸምለታል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ሃይማኖትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ በሃይማኖትም ሕግ ታዝዘው ለጣዖት መስገድን እምቢ አሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ከእሳት ቢጣሉ በሃይማኖት የእሳትን ኃይል አጠፉ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በሃይማኖት የአናብስትን አፍ ዘጋ፡፡ ጌዴዎን ያለ ጦር መሣሪያ አእላፍ የአሕዛብን ሠራዊት ድል አደረገ፡፡ ይህ የሃይማኖትን ታላቅነት ያስረዳል (ዕብ.፲፩፥፴፫-፴፬)፡፡ በአዋልድ መጻሕፍትም አቡነ ኤውስጣቴዎስ በአጽፋቸው (በመጎናጸፊያቸው) ባሕር ሲከፍሉ፣ ፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከንብ ቀፎ ተከተው በቆዳ ተጠቅልለው ከተወረወሩበት ገደል ሲወጡ፣ ከእሳት መካከል ቆመው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፤ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚቆራርጥ መርዝ ሲያጠጡት ሕያው ሆኖ የሚያሳየን የሃይማኖትን ታላቅነት ነው፡፡
በአሥራውም ሆነ በአዋልድ መጻሕፍት የተጠቀሱት ሰዎች ታላላቅ ተአምራት ሲፈጽሙ የምንመለከተው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “አማን አማን እብለክሙ ዘየአምን ብየ ዘአነ እገብር ውእቱሂ ይገብር ወዘየዐቢ ይገብር፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤” ያለው ቃል ተፈጽሞላቸው ነው፡፡(ዮሐ.፲፬፥፲፪)፡፡
ረ. የሃይማኖትሰዎች ያደረጓቸውን ልዩ ልዩ ተጋድሎዎችን መግለጥ፡- እግዚአብሔር ድንቅ የሆነ ሥራውን ለፍጥረቱ የሚሠራው በፍጥረቱ አማካኝነት ነው፡፡ ይህም በልዩ ልዩ መንገድ ይፈጸማል፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ በስፋትና በግልጥ ከሚሠራባቸው ፍጡራን መካከል ደግሞ ቅዱሳን ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ለሕገ እግዚአብሔር ተገዝተው ፈቃዱን በመፈጸማቸው ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ አደረጉ፡፡ በዚህ ሰውነታቸውም ከእግዚአብሔር በተቀበሉት ኃይል ብዙ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ የአሥራውም ሆኑ አዋልድ መጻሕፍት ይህን የቅዱሳንን የተጋድሎ ሕይወት ይገልጣሉ፡፡ ነሕምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መሥራቱ፣ አስቴር በጾም በጸሎት ሕዝበ እሥራኤልን ስለመታደጓ፣ ዮዲት በጥበብ ሆሊፎርንስን መግደሏ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው ሕሙማንን መፈወሱ፣ እመቤታችን፣ጻድቃን ሰማእታት ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት መፈጸማቸው በየቅዱሳት መጻሕፍቱ ተገልጦ እናገኛለን፡፡
አዋልድ መጻሕፍትን ቤተ ክርስቲያን የምትቀበለው እንዴት ነው?
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍትን የምትቀበልበት ሥርዓት አላት፡፡ ቀደም ተብሎ በተደጋጋሚ እንደተገለጠው የአዋልድ መጻሕፍት ልጅነታቸው በይዘት፣በመንፈስ፣ በምሥጢርና በመሠረተ ሐሳብ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት “አሥራው መጻሕፍት” ይባላሉ፡፡ አሥራው ማለት ሥሮች ማለት ሲሆን፣ አሥራው መጻሕፍት ሲላቸው ደግሞ የሌሎች መጻሕፍት መገኛዎች፣ ሥሮች ማለት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ማለት ለአዋልድ መጻሕፍት በይዘትና በመንፈስ፣ በምሥጢርና በመሠረተ ሐሳብ አስገኚ ሥራቸውና ወላጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ኾኖ በእርሱ ሥርነት የሚበቅሉና የሚያድጉ ማለት ነው፡፡
ይህ ኾኖ ሳለ በአንዳንድ ይዘታቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ቢመስሉም ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ፣በጌታችን ከተገለጠውና ከሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ ከመጣው የቤተክርስቲያንእምነትና ትምህርት ጋር ተቃርኖ ያላቸውን መጻሕፍት ቤተ ክርስቲያን ታወግዛለች እንጂ አትቀበልም፡፡ መጻሕፍቱም “ዲቃሎች” እንጂ “አዋልድ” አይባሉም፡፡
አዋልድ መጻሕፍትን በተመለከተ በሚከተሉት ነጥቦች መለየት እንደሚቻል ሕንዳዊው የነገረ መለኮት ሊቅ ጢሞቴዎስ አለን ይገልጡታል፡-
- ዓላማቸው መንግሥተ እግዚአብሔር የሆነ፣
- በሃሳብ፣ በመንፈስ፣ በምሥጢር፣ በነገረ መለኮት ከአሥራው መጻሕፍትና ከቅዱሳት የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር የማይጋጩ፣
- ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ሕይወትና አኗኗር ተስማሚ የሆኑ፣
- የቤተ ክርስቲያን አበው፣ትውፊት ወይም ጉዞ ምስክር ያላቸው፣
- ውስጣዊ ተቃርኖ የሌለባቸው፡፡
እንግዲህ በጎ ትምህርት የሚያስተምሩንን፣ ስለ ቅዱሳን አበውና እመው ሃይማኖታዊ ተጋድሎ የምንረዳባቸውን፣ አሥራው መጻሕፍትንም የሚያብራሩልንና የሚተረጉሙልንን አዋልድ መጻሕፍትን በመጠቀም በሃይማኖት ለመጽናት፣ በጎ ሥራ ለመሥራት ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን!
“መንፈሰ እግዚአብሔር ያለበት፣ ሰውን ከክፋት፣ ከኃጢአት፣ ከበደል የሚመልስ፤ ይልቁንም ሃይማኖቱን የሚያጸናለት መጽሐፍ ከእግዚአብሔር ነውና ይጠቅማል” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ቃል ያስተላለፈው ለጊዜው በሃይማኖት ትምህርት ወልዶ ላሳደገው ለደቀመዝሙሩ ጢሞቴዎስ ቢኾንም ፍጻሜው ግን እስከ ሕልፈተ ዓለም ለሚነሡ ክርስቲያኖች ሁሉ የተናገረው ነው፡፡ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (፪ኛ. ጢሞ.፫፥፲፮-፲፯)
መንፈሰ እግዚአብሔር ያለባቸው መጻሕፍት ሁሉ እንደሚጠቅሙና እንደሚያስፈልጉ ሐዋርያው በመልእክቱ ያስተላለፈውን ቃል መመሪያ አድርጋ ቅድስት ቤተክርስቲያንየአሥራው መጻሕፍት ልጆች የምንላቸውን አዋልድ መጻሕፍትን አዘጋጅታልናለች፡፡ አዋልድ መጻሕፍት፡-
“አዋልድ መጻሕፍት” የሁለት ቃላት ጥምር ሐረግ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ የመጻሕፍት ልጆች ማለት ነው፡፡ መጻሕፍት የተባሉትም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተለይተውና ተቆጥረው የምናውቃቸው ሰማንያ አንዱ መጻሕፍተ ብሉያትና ሐዲሳት ናቸው፡፡
አዋልድ መጻሕፍት የአሥራው መጻሕፍት ምሥጢር ትርጓሜ ተብራርቶ የሚገኝባቸው መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቅዱሳን ነብያት እንዲሁም ሐዋርያት፤ በየዘመናቱ የተነሡ መምህራንና ሊቃውንት አዋልድ መጻሕፍት መጠቀማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ /ኢያሱ 10፤13, 2ኛ ሳሙ.1፤18/ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት አዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊ ናቸው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ‹ሕግን አውቃለሁ›ለሚል ሰው ወንበዴዎች ደብድበው በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ስለሄዱ አንድ መንገደኛ በምሳሌ አስተምሮታል፡፡ ይህን ቁስለኛ አንድ ሩኅሩኅ ሳምራዊ ወደ እንግዳ ማረፊያ ቤት ወስዶ ከጠበቀው በኋላ ለእንግዶች ማደረፊያ ቤት ጠባቂውሁለት ዲናር አውጥቶሰጠውና፤ “ጠብቀው፥ ከዚህ በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው፡፡(ሉቃ.፲፥፴-፴፭) ይህ ምሳሌ ነው፡፡ በወንበዴዎች የቆሰለው ቁስለኛ፤ በኃጢአት መርዝ የተለከፈና የቆሰለ የሰው ልጅ ሁሉ ሲሆን፤ ወንበዴው ደግሞ ዲያብሎስ ነው፡፡
የአዳምን ቁስል የፈወሰው ርኁሩኁ ሳምራዊ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ይህን ቁስለኛ ያሳደረበት የእንግዶች ማረፊያ ቤት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት (መዝ.፴፰፥፲፪፣ዘፍ.፵፯፥፱)፡፡ የእንግዶች ማረፊያ ቤት (የቤተ ክርስቲያን) ጠባቂዎች የተባሉት ደግሞ አባቶቻችን መምህራን ናቸው፡፡ (የሐዋ.፳፥፳፰) ራሱን በሩኅሩኁ ሳምራዊ የመሰለው ጌታችን ለቤተ ክርስቲያን መምህራን የሰጣቸው ሁለት ዲናር የተባሉት መጻሕፍተ ብሉያትና መጻሕፍተ ሐዲሳት ናቸው፡፡ ሁለቱን ዲናር ከሰጠ በኋላበነዚያ ብቻ ሳይወሰን “ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ” አለው፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው በሁለቱ ዲናሮች (በብሉያትና ሐዲሳት) ተመሥርተው የረቀቀውን አጉልተው፣ የተሠወረውን ምሥጢር ገልጠው ምእመናንን የሚያስረዱ ልዩ ልዩ የትርጓሜ፣ የምክር፣ የተግሳጽ፣ የታሪክና የመሳሰሉትን መጻሕፍትን ጽፈው እንዲያስተምሩና እነዚህም ተጨማሪ መጻሕፍት በመጻፋቸው የድካማቸው ዋጋ እንደማይጠፋባቸው ሲገልጽ ነው፡፡ “እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ” ማለቱ በዳግም ምጽአቱ የድካማቸውን ዋጋ እንደሚከፍላቸው ያሳያል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዮስ አስቀድመን መከራ ተቀበልን ተንገላታንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን፡፡” (፩ኛ.ተሰ.፪፥፲፪) ብሏል፡፡ ገድል ያለው መከራውን ነው፡፡
የአዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊነት፡-
ፍቁረ እግዚእ የተባለ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤” ካለ በኋላ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ባልበቃቸው ይመስለኛል” (ዮሐ.፳፥፴፤፳፩፥፳፭) በማለት ተናግሯል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሲመላለስ ያደረጋቸው ተአምራት እያንዳንዳቸው እንዳልተመዘገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በአጽንዖት አስረድቷል፡፡
በሌላ በኩል ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”በማለት የአዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊነት ምን እንደሆነ ገልጦ ተናግሯል፡፡
በዚህ የተነሣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በልዩ ልዩ ጊዜና ቦታ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ሲጽፉ አዋልድ መጻሕፍትን ለትርጓሜ፣ ለምክር፣ ለተግሳጽ፣ ለታሪክ አስረጂነት እንደተጠቀሙባቸው አስረድተዋል፡፡ (ኢያ. ፲፥፲፫፤ ፩ኛ.ሳሙ .፩፥፲፰፤ ይሁ.፱)
እንግዲህ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ከታነጽን በእነርሱ መንገድ መመራት ያሻናል፡፡ አዋልድ መጽሐፍቱ ከትምህርት ሰጪነት ባሻገርበእለት እለት ሕይወታችንለጸሎት የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡ በገመድ ያለ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈካውና የሚታየው በአምፖል ሲበራ እንደሆነ ሁሉ በአሥራው መጻሕፍት የሚገኝ ጥበብ፣ ትምህርትና ምሥጢርም የሚረዳው የሚገለጠው በአዋልድ መጻሕፍት ተብራርቶ ሲታይ ነው፡፡
ወስብሐትለእግዚአብሔር!