ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና ትስስሮች በቤተክርስቲያናችን አገልግሎት፤
ምእመናን በሃይማኖት የጸኑ፣ በምግባር የቀኑ ይሆኑ ዘንድ በመተሳሰብ፤ በሞራል፤ በአብሮነትና፤ በማህበራዊ ትስስር ሊደገፉ ይገባል፡፡ የበጎ አድራጎት መነሻው ቅዱሳት መጻሕፍት ሲሆኑ በኅብረተሰቡ መካከል መተሳሰብን፤አብሮነትን፤ እና ሰብአዊ ርህራሄን ከማጎልበት ባሻገር ለነፍስ ዋጋ የሚያሰጡ ትምህርቶችንም የያዙ ናቸው፡፡ ስለሆነም የመንፈስዊ አገልግሎት ዋጋ ከመስጠቱም ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ የመተሳሰብና የሰብአዊ ርኅራኄ መንፈስ ማዳበር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑት ስልቶች መካከል ምእመናችንን ማስተማር፤ ማደራጀት፤ ማስተባበር ናቸው፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መነሻውም ሃይማኖት ነው፡፡
ለምሳሌ ሃገር ቤት በገጠሩ አካባቢ በስፋት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በድንገት ሀብት ንብረቱ ቢቃጠልበት ርዳታ ያደርጉለታል፡፡ እንዲሁም ጧሪ ዘመድ ሳይኖረውና የሚሠራ ጉልበቱ ሲደክም ከቤታቸው በማስቀመጥ ተፈራርቀው ይጦሩታል፡፡ ይህም ተግባር መጽሐፍ ቅድሳዊ ተግባር በመሆኑ በሕዝቡ አኗኗር ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደሩ ለዚህ ድርጊት የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦና ድርሻ ከፍተኛ ነው ::
ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት፤ ለመተሳሰብ፤ ለመረዳዳት፤በችግር ጊዜ ለመደራረስ፤ እንዲሁም ባጠቃላይ የመንፈሳዊ አብሮነት ጥንካሬ ለማዳበር ምሳሌ ከሚሆኑ መሳሪያዎቻችን መካከል ዝክሮች፣ ሰንበቴዎች፤ ማኅበሮችና የመናፈሻ ቦታ ጊዜዎች (ባርቤኪው) ወዘተ በስፋት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የተቀደሱና ጠናካራ ትውፊቶች የበጎ አገልግሎት ለመሰጠት አመቺ ስለሆኑ ቤተክርስቲያናችንም እነዚህን ስልቶች በመጠቀም የሚከተሉትን የበጎ ፈቃድ ማህበራዊ ትስስር አገልግሎቶችን ከመንፈሳዊ ጎን ለጎን ታከናውናለች ፡፡
- ሳምንታዊ ዝክር የልማትና ማህበራዊ ማስተባበሪያ ክፍሉ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት፤
- በአመት ሶስቴ የመስከረም፤ የህዳርና የሰኔ ማርያም ዝክር የልማትና ማህበራዊ ማስተባበሪያ ክፍሉ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት፤
- በየወሩ የህጻናት የማርያም ጽዋ ማህበር የሰንበት የህጻናት ክፍሉ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት፤
- በአመት ሁለቴ በበጋ ወር የሚደረግ የባርቤኪው ፕሮግራም የልማትና ማህበራዊ ማስተባበሪያ ክፍሉ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት፤
- ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለን ግንኙነት ጠንካራ በመሆኑ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አባቶችና ምእመናን አንድ ላይ በመሰባሰብ በጋራ በቤተክርስቲያናችን ቅጥር ግቢ ውስጥ የደመራ በአልን በደማቁ ስናከብር፤ ጥምቀትን ደሞ ኦታዋ በሚገነው በደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በመሰባሰብ እናከብራለን።
እግዚሃብሄር አንድነታችንንና መተሳሰባችንን እስከ መጨረሻው ያጠንክርልን!
ሰኔ 2020